ወገናዊ የታሪክ – ድርሰት

ይህ ፅሑፍ፤ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” እና “አዳፍኔ” በሚሉ ርዕሶች ባሳተሟቸው ሁለት መጻህፍት ባነሷቸው አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ጥቂት ነጥቦችን በማንሳት የግል አስተያየቴን ለመስጠት የተሰናዳ ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የፕሮፌሰር መስፍን ሥራዎች በትውልዶች ዘንድ ጠንክሮ የመስራት ስሜትን የሚቀሰቅስና የማይበርድ ቁጭት ሊያጭር የሚችል ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን፤ ‹‹ታሪክ ምንድን ነው?›› የሚለው ጥያቄ ከጥንካሬ፤ ከትጉሕነት፤ ከአብሮ መኖርና ከህልውና ጋር በማያያዝ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ቃላትን በመደርደር እንዲህ በማለት ይገልጹታል፡-

“ታሪክ የህዝብ፤ የተከታታይ ትውልዶች ሥራ ነው፤ ኑሮ ነው፤ ትግል ነው፤ ተጋድሎ ነው፤እያንዳንዱ የቀደመው ትውልድ ህብረቱን፣ ንብረቱንና መብቱን፤ በአጠቃላይ የአብሮ መኖር ህልናውን አረጋግጦ ለሚቀጥለው ትውልድ ያስተላለፈውንና ያስተላለፈበትን ሁኔታ ጭምር የሚገልጽ ቅርስ ነው፤ ተከታዩ ትውልድ ከቀደመው ትውልድ የተረከበውንና ራሱ ደግሞ የጨመረውን እያካተተ የሚተርክ ዘገባ ነው” (መክሽፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ 34)፡፡

የአንድ ሃገር ህዝብ፤ ምን ጊዜም ቢሆን የሃገሩን ጉዳይ “ይመለከተኛል” በሚል ስሜት መመልከትና እንደ ዜጋ የሚገባውን ሁሉ ለሃገሩ ማድረግ እንዳለበት የፕሮፌሰር ጽኑዕ እምነት ነው፡፡ እኔም ይህን እምነት ሙሉ በሙሉ እጋራለሁ፡፡ ለሃገር የሚከፈል ዋጋ ገደብ የለውም፡፡ ለሃገር የሚከፈል ዋጋ መጠንና ልኬት ሊኖረው አይገባም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ የአንድ ሃገር ዜጋ በየተሰማራበት የሥራ መስክ በትጋት መስራት አለበት፡፡ በሃገሩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ የሩቅ ተመልካች ሊሆን አይገባም፡፡ አንዳንዶች እንደሚያደርጉት፤ ባሕር ማዶ ሆኖ የሐገርን ጉዳይ በዝምታ መመልከት ወይም እንዲሁ መጮህ ሳይሆን፤ በቅርበት ሆኖ አገሪቷ የምትጠይቀውን ዋጋ መክፈል አለበት፡፡ በሃገሩ የአስተዳደርና የፍትሕ ጉዳይ ተመልካች መሆን ሳይሆን፤ “ይመለከተኛል” በሚል ስሜት ጉዳዩን በሚገባ መከታተል፣ መተቸትና ጣልቃ መግባት እንዳለበት እሙን ነው፡፡
“The good citizen, who behaves himself and votes regularly, is no longer good enough.…..He must know how his government really operates, what interests and forces are behind particular policies, what the results of such polices are likely to be,….”(Rodee, Anderson and Christol (1957) introduction to political science).
የአንድ ዜጋ ግዴታና ትጋት እስከዚህ መድረስ እንዳለበት እኔም አምናለሁ፡፡ ሆኖም እኛ ኢትዮጵያውያን፤ በተለያዩ ምክንያቶችና ጫናዎች የተነሳ አብዛኛውን ጊዜ የዜግነት ግዴታችንን እንደማንወጣ ሁሉ፤ በዜግነት መብታችንም አንጠቀምም፡፡ ግዴታችንን ካልተወጣን፤በመብታችን ላንጠቀም እንችላለን፡፡

በእርግጥ፤ የዜግነት ግዴታን በመውጣት በመብት በመጠቀም ረገድ ከባድ ዋጋ የሚያስከፍሉ ሁኔታዎች እንዳሉ አልክድም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን በሃገራችን ጉዳዮች ተመልካች መሆን እንሻለን፡፡ የተለያዩ ሰበባ ሰበብ በመፍጠር የሚጠበቅብንን ነገር ሁሉ (በክህሎትም ሆነ በዕውቀት ረገድ) አሟልተን አንፈጽምም፡፡ ከሰራንም ብዙ ጎደሎዎች ይኖራሉ፡፡ የምናከናውናቸው ሥራዎች በግድየለሽነትና በደንታ ቢስነት የሚሰሩ ሥራዎች ይሆናሉ፡፡
ስለዚህ በጉልበት የሚነጥቁንም እንዳለ ሆኖ፤ በስንፍናችን ግዴታችንንም ሆነ መብታችንን ለሌሎች ሰዎች አሳልፈን እንሰጣለን፡፡ የህዝብ መብት በጉልበት ለሚነጥቁ መታገል ሲገባን፤ ችላ በማለት የነጣቂዎች የጭካኔያቸውን አድማስ እናሰፋላቸዋለን፡፡ ግዴታችንን እየተወጣን መብታችንን ማስከበር፤ መብታችንን የሚጋፋ ሲገጥመንም መታገል ለማንም የሚተው ኃላፊነት አይደለም፡፡

ስለዚህ በሃገራችን ጉዳይ በተመልካችነት ሳይሆን፤ በ“ይመለከተኛል” ስሜት የሚገባውን ሁሉ ማድረግ ካልቻልን፤ ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት፣ ማደግና መሻሻል ሳይሆን መበስበስ እና በስብሶ መፈራረስ ይጠብቀናል። ይህም የታሪክ ክሽፈት ይሆናል፡፡ በተጨማሪም፤ አንድ ትውልድ ካለፈው ትውልድ የተረከበውን ታሪክ ጠብቆና የራሱ አስተዋጽኦ ጨምሮ ለሚቀጥለው ትውልድ ካላስተላለፈ ከታሪክ ክሽፈት ማምለጥ እንደማይቻል ፕሮፌሰር መስፍን ይነግሩናል፡፡ በዚህ ረገድ፤ “መክሽፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል ፕሮፌሰር መስፍን ባሳተሙት መጽሐፍ ላይ አስተያየት የሰጡ ግለሰቦች በጠንካራ ጎን ያነሷቸውን ነገሮች እጋራለሁ፡፡

ሆኖም የአጼ ዮሐንስን ሰብዕና፤ በተለይም ስለውጭ ወራሪዎች (ቅኝ ገዢዎች) ነበራቸው ያሉትን አመለካከት ለመቀበል ያስቸግረኛል፡፡ አጼ ዮሐንስ ከውጭ ወራሪዎች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት በተመለከተ ከትክክለኛ ታሪካቸው በተለየ መልኩ የቀረቡ ጉዳዮች፤ ከላይ በተጠቀሱት የፕሮፌሰር መስፍን መጻሕፍት ውስጥ ስላነበብኩ ጥቂት ነጥቦችን አንስቼ አስተያየት መስጠት እሻለሁ፡፡

“የአገርን ህልውና መጠበቁ የነገስታቱና የሕዝቡ ዋና ተግባር ሆኖ ምዕተ-ዓመታት ተቆጠሩ፤ ህዝቡ ህልውናን የሚጠብቀውን ጀግንነትና አርበኝነትን እያወደሰና እያሞገሰ፤ እየሸለመና እያከበረ መኖርን ባህሉ አደረገ፤…… አባ በዝብዝ ካሳ ይህንን የቆየውን የህልውና ሕግ ሽረውታል፤ አንድ ጊዜ አይደለም፤ ሁለት ጊዜ፤መጀመሪያ አጼ ቴዎድሮስን ሊወጋ የሚጓዘውን የእንግሊዝ ጦር ግዛታቸውን አቋርጦ ወደ መቅደላ ሲጓዝ እያስተናገዱና መንገድ እየመሩ የአገርንና የሕዝብን ህልውና ደረጃ ዝቅ አድርገው….፡፡ በዝብዝ ካሳ ነጉሠነገሥት ከሆኑም በኋላ…. ለሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የብረት አጥር ሆነው የቆዩትን ጀግና፤ ራስ አሉላ አባነጋን ገሸሽ በማድረጋቸው የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል በር ለኢጣልያኖች ከፍቷል…”(ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም፤አዳፍኔ፤ ፍርሃትና መክሸፍ፤ 2007 ዓ.ም፤ ገጽ 8-10)፡፡

ከዚያም ፕሮፌሰር መስፍን እንዲህ በማለት ይቀጥላሉ፡- “ብሪታንያ አጼ ቴዎድሮስን ስትወጋ የደጃዝማች ካሳን (በኋላ አጼ ዮሐንስ) ሙሉ ትብብር አግኝታ ነው፤ ይህ የደጃዝማች ካሳ (አጼ ዮሐንስ) ከውጭ ጠላት ጋር ተባብሮ ወገንን ማስጠቃት በዚያ አካባቢ የተለመደ ነበር….”(ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም፤2005 ዓ.ም፤ መክሽፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ ፣ ገጽ 105)፡፡

እዚህ ላይ ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡ ለመሆኑ፤ እንግሊዞች አጼ ቴዎድሮስን ለመውጋትና ሃገራችንን ለመድፈር የተነሳሱት የማንን ትብብር አግኝተው ነው? ብለን ከጠየቅን፤ አንደኛ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ራሳቸው አጼ ቴዎድሮስ ናቸው፡፡ ምክንያቱም አጼ ቴዎድሮስ፤ ነገሩን በዲፕሎማሲ በመፍታት ፋንታ፤ አላግባብ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ የእንግሊዝ (የአውሮፓ) ዜጎችን ማሰራቸው ነው፡፡

እንግሊዞች አጼ ቴዎድሮስን ለመውጋት የወሰኑት፤ ንጉሱ የተፈጠረውን አለመግባባት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ፈቃደኛ ስላልሆኑና ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የሚሰሩ ‹‹የእደ ጥበብ ባለሙያዎች ካልተላከልኝ›› በማለት እንግሊዛዊ የቆንስላና የሚሲዮን አባሎችን በግፍ በማሰራቸው ነበር፡፡
በተጨማሪም፤ እንግሊዞች የንጉስ ምኒልክን (በኋላ አጼ ምኒልክ) እና የዋግ ሹም ጎበዜ ( በኋላ አጼ ተክለ ጊዮርጊስ) ትብብርና አይዞህ ባይነት አግኝተው ነው። እንግሊዞች አጼ ቴዎድሮስን ለመውጋት ወደ ሃገራችን ሲገቡ፤ እንግሊዞችን በመርዳትና በመተባበር ብቻ ሳይወሰኑ፤ አጼ ቴዎድሮስን በመውጋት ጭምር የታሰሩ የእንግሊዞች ዜጎችን ለማስለቀቅ ወደ መቅደላ የዘመቻ ሙከራ ያደረጉት ንጉስ ምኒልክና ዋግ ሹም ጎበዜ ነበሩ (መምህር ገ/ኪዳን ደስታ፤ 2005 ዓ.ም፤ ‹‹እምቢታ አንፃር ወረርቲ››፤ ገፅ 107-108፤ ከዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴ ካልታተመ ጽሑፍ ወስደዋል)፡፡
በተለይ ንጉስ ምኒልክ አጼ ቴዎድሮስን ለመውጋት (እንግሊዞችን ለመርዳት) ወደ መቅደላ ተደጋጋሚ የዘመቻ ሙከራ ከማድረጋቸውም ባሻገር፤ በአጼ ቴዎድሮስ መሞት መደሰታቸውን ለንግስት ቪክቶርያ እንዲህ በማለት ገልጸዋል፤ ‹‹…እኔ፡ እራሴ፡ ወደ፡ መቅደላ፡ ዘምቼ፡የታሰሩትን፡ ሰዎችሽን፡ ለማስፈታት፡ ነገሩ፡ ባይመችኝ፡ ተመልሼ፡ አገሬ፡ ገባሁ፡፡ ደግሞ፡ ሁለተኛ፡ ሰዌን፡አዝምቼ፡ የናንተ፡ ወሬ፡ ቢርቀው፡ ያገሬ፡ ሰው፡ ፋሲካን፡ ከዘመቻ፡ መዋል፡ አለመደምና፡ ተመልሶ፡ ገባ፡ሰዌ፡ በገባ፡ በ፲ ቀን፡ እንግሊዞች ድል አደረጉ፡ ቴዎድሮስ፡ ሞቱ፡ የሚል፡ የምስራች፡ መጣልኝ፡፡ ይህን፡ብሰማ፡ እጅግ፡ ደስ፡ አለኝ…፡፡›› (ተክለ ጻድቅ መኵሪያ፤ 1982 ዓ.ም፤ አጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት፤ ገጽ 69)

እንግሊዞች፤ ደጃዝማች ካሳ አባ በዝብዝን የተመለከተ ብዙ መረጃ ስላልነበራቸው ወደ ሃገራችን እስኪጠጉ ድረስ ግንኙነታቸው ከንጉስ ምኒልክና ከዋግ ሹም ጎበዜ ጋር ነበር፡፡ ሆኖም፤ እንግሊዞች የደጃዝማች ካሳ አባ በዝብዝን አቅምና አቋም ካወቁ በኋላ፤ በመጀመሪያ መልዕክተኞችን በመላክ፤ ቀጥሎም በጀነራል ናፒር አማካኝነት ስለዘመቻው ዓላማ ከደጃዝማች ካሳ ጋር ተነጋግረዋል። በዚህ ጊዜ፤ ደጃዝማች ካሳ አባ በዝብዝ፤ ‹‹ዜጎቻችሁን ለማስፈታት የምታደርጉትን ጥረት አንቃወምም። ነገር ግን ወደ ሃገራችን ከገባችሁ በኋላ አንወጣም ብትሉስ ምን ዋስትና አለን?›› ሲሉ ለእንግሊዞች ጥያቄ አቅርበውላቸው ነበር፡፡ እንዲሁም፤ ‹‹ግብጻውያን ባገራችን ላይ በሚያደርጉት ተጽዕኖ እንዳትረዷቸው፤ ቆንሲልም እንዳትሸሙብን ማረጋገጫ ስጡን›› ብለዋቸው ነበር፡፡

እንግሊዞችም ወደኢትዮጵያ የመጡበት ዓላማ፤ የታሰሩ ዜጎቻቸውን ለማስፈታት ብቻ መሆኑን እና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገቡ በአዋጅ እንደሚያረጋግጡላቸው ተስማምተው ነበር፡፡ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ገዝተው ለመጠቀም ትብብር እንዲደረግላቸውም እንግሊዞች ጥያቄ ማቅረባቸው ተዘግቧል (መምህር ገ/ኪዳን ደስታ፤ 2005 ዓ.ም)፡፡

ሆኖም ‹‹ከውጭ ጠላት ጋር በመተባበር ወገንን ማስጠቃት በዚያ አካባቢ የተለመደ ነው” ሲባል (በቁጥር ባይገለጥም)፤ ደጃዝማች ካሳ (አጼ ዮሐንስ) ከውጭ ጠላት ጋር ተባብረው ብዙ ጊዜ ወገንን ያስጠቁ ነበር ለማለት እንደሆነ መገንዘብ አያስቸግርም፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው፤ እንግሊዞች እስረኞቻቸውን ለማስፈታት ሲመጡ፤ ደጃዝማች ካሳ ከመፍቀድ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡
ሆኖም አጼ ዮሐንስን፤ እንደ ምኒልክ (ከመንገሳቸው በፊትም ሆነ በኋላ) ከውጭ ጠላት ጋር በምስጢርም ሆነ በገሃድ ውል በማድረግና ግንባር በመፍጠር ወገንን በማስጠቃት፤ ሀገርን በማሰለልና በማስደፈር ወይም በማስወረር የሚገለጽ ተግባር አልነበራቸውም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ፤ አጼ ዮሓንስ፤ ወገንን አስተባብሮ ሃገርን ከወራሪ በመጠበቅ የሚገለጽና በገሃድ የሚታወቅ ታሪክ ነበራቸው፡፡

ለምሳሌ፤ ራሳቸው በሰሜን ኢትዮጵያ (ምጽዋ) የመጡ ጠላቶችን እየተከላከሉ ‹‹….አንተ ወደ እኔ መምጣት የለብህም፤ ለጊዜው አንተ የባህር መንገድ መዝጋት አለብህ፤ በአውሣ በኩልም ሆነ በጨርጨር ዘይላ በኩል ማንንም ሰው ማሳለፍ የለብህም፤ …. እኛ ሁለታችን አንድ ሆነን ከኖርን፤ በእግዚአብሔር ብርታት እንኳንስ እነዚህን ደካማ ጣልያኖች የሌላ ሃገር ኃይለኛ ዜጎችንም እናሸንፋችዋለን›› በማለት ምስራቃዊና ደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍልን የመከላከል ኃላፊነቱን ለንጉስ ምኒልክ ሲሰጡ፤የሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍልን የመጠበቅ ኃላፊነቱን ደግሞ ለንጉስ ተክለ ሃይማኖት በመስጠት ሌሎችም እንዲረዷቸው ያደርጉ ነበር፡፡

በመሆኑም፤ ፕሮፌሰር መስፍን ‹‹…..ይህ የደጃዝማች ካሳ (አጼ ዮሐንስ) ከውጭ ጠላት ጋር ተባብሮ ወገንን ማስጠቃት በዚያ አከባቢ የተለመደ ነበር….” ሲሉ፤ ጠላትና ወገን መለየት ስላልቻሉ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከህሊናቸው ቁጥጥር በላቀ ስሜት እየተነዱ ሐሳባቸውን ለመግለጽ የተገደዱ ይመስላል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ከዚሁ ጋር አያይዘው የሚከተለውን ይላሉ፤‹‹….እንዳጋጣሚ ሆኖ የእንግሊዞች ዓላማ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሳይሆን በአጼ ቴዎድሮስ ላይ ብቻ የተቃጣ ስለነበረ ኢትዮጵያ ተረፈች”፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን፤ ‹‹የእንግሊዞች ዓላማ በአጼ ቴዎድሮስ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነበር›› ሲሉ ያቀረቡትን ድምዳሜ፤ እንግሊዞች በወቅቱ ከነበራቸው ቅኝ ግዛትን የማስፋፋት ፍላጎት ጋር ተነፃጽሮ ሲታይ ለማመን ያስቸግራል፡፡ እንዲያውም፤ አቶ ተስፋ ሚካኤል ትኩእ “ሀገሬ፤ የህይወቴ ጥሪ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት ግለ ታሪካቸው የጠቀሱት አንድ ጉዳይ አለ፡፡ እኚሁ ፀሐፊ፤ “በ1861 ዓ.ም፤ ከእንግሊዝ ንግስት ቪክቶሪያ፤ ለጀነራል ሮበርቶ ናፔር የተላለፈለት ትዕዛዝ፤ አጼ ቴዎድሮስን በሕይታቸው ሳሉ በጥንቃቄ ይዞ እንዲያመጣ ነበር። ንግስት ቪክቶሪያ በስሟ ኢትዮጵያን ለመግዛት ነበር ያሰበችው” ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል፤ እንግሊዞች የታሰሩት ዜጎቻቸውን አስለቅቀው እንደሚወጡ ለአጼ ዮሐንስ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ከእንግሊዞች ጋር በተደረገው ድርድር አረጋግጠውላቸው ነበር፡፡ እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ሌላም ጉዳይ አለ፡፡ ምንም እንኳ እንደ አጼ ዮሐንስ ተደራድረው ማረጋገጫ ባያገኙም፤የንጉስ ምኒልክና የዋግ ሹም ጎበዜ ምኞት ከአጼ ቴዎድሮስ ውድቀት በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መሆን ነበር፡፡ ስለዚህ እንግሊዞች የታሰሩ ዜጎቻቸውን አስለቅቀው ከመቅደላ እንደሚመለሱ ለንጉስ ምኒልክና ለዋግ ሹም ጎበዜ ጭምር ግልጽ እንደ ነበር አያጠራጥርም፡፡ እንግሊዞች ከመቅደ ላካልወጡ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መሆን እንደማይቻል ግልጽ ነው።

ፕሮፌሰር መስፍን “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ሲሉ በሰየሙት መጽሓፋቸው፤ የአጼ ምኒልክ የውጫሌ ውል ከአጼ ዮሓንስ የሂወት ውል ጋር ያነጻጽራሉ፡፡ እነዚህን ሁለት ውሎች ሲያነጻጽሩ፤ “አጼ ዮሓንስ ከብሪታንያ ጋር ከአደረጉት የሂወት ውል ከሚባለው ጋር የሚመሳሰል የማታለል ዓላማ ነበረበት…” (ገጽ፣ 123) በማለት ሃገርን ለመሸጥ የተደረገ ውልን ሃገርን ለማስመለስ ከተደረገ ውል ጋር ለማመሳሰል መሞከራቸው የውገና ታሪክ ከማለት ውጭ ምንም ሊባል አይችልም፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን፤ አጼ ዮሓንስን በሂወት ውል ጥፋተኛ የሚያደርጓቸው፤ የግብጽ ወታደሮችን ከሱዳን ማህዲስቶች ጥቃት ለማዳን በተደረገ ጦርነት በሞቱ ዜጎቻችን ነው፡፡ የሂወት ውል፤ ኢትዮጵያ ሸቀጦችንና የጦር መሳሪያዎችን ጭምር በምጽዋ ወደብ በነጻ ማስወጣትና ማስገባት እንድትችል፤ እንዲሁም ቦገስን ለማስመለስ በአጼ ዮሓንስና በእንግሊዝ መካከል የተደረገ ውል እንደነበር ተገልጿል (ተክለ ጻድቅ መኵሪያ፤ 1982 ዓ.ም፤ አጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት፤ ገጽ 273-4)፡፡

ይህ ውል ከመፈረሙ ቀደም ሲል፤ በወቅቱ በቱርኮች እጅ የነበረችው ምጽዋ የኢትዮጵያ እንደነበረች በማስረዳት፤ የምጽዋ ወደብ ለኢትዮጵያ እንዲመለስ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ አጼ ዮሓንስ ባቀረቡት በዚህ ጥያቄ መሰረት፤ አንድ የእንግሊዝ ሚኒስትር ‹‹ምጽዋን ለኢትዮጵያ መስጠቱ ተገቢ ነው›› በማለት፤ በወቅቱ የግብጽ የበላይ ተቆጣጣሪ ለነበሩት የእንግሊዝ መንግስት ተወካይና ለቱርክ መንግስት ይጠቁሙ እንደነበር ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴ ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ጉዳይ በእንግሊዝ አገር ተመዝግቦ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ በዚህም መሰረት፤ ኢትዮጵያ የቦገስን መሬትና ከረን ላይ የነበረውን የጦር መሳሪያና ስንቅ ከግብጾች መረከቧን ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ይገልጻሉ (ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴ፤ 2007 ዓም፤ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግጭት፤ መንሥኤ እና መፍትሔ፤ ገጽ፤ 94-5)፡፡

ያም ሆነ ይህ፤ አጼ ዮሓንስ ከአክሱም መንግስት ወድቀት በኋላ ለብዙ ዘመናት በውጭ ኃይሎች ይተዳደሩ የነበሩ እንደ እነምፅዋ ያሉ ቦታዎችን ለማስመለስ ሳይታክቱ እየሰሩ ያለፉ መሪ መሆናቸውም መዘንጋት የለበትም፡፡ በዚህም መሰረት፤ አጼ ዮሓንስ ግዴታቸውን ከተወጡ (የግብጽ ወታደሮች ካስለቀቁ) በኋላ በውላቸው መሰረት ተፈጻሚ እንዲሆንላቸው እንግሊዝን እየጠየቁ ሳለ ሞት ቀድሟቸዋል፡፡ ተተኪያቸው (አጼ ምኒልክ) ውሉ ተፈጻሚ እንዲሆንላቸው መጠየቅና የአጼ ዮሓንስን ሌሎች ጅምር ሥራዎች ማስቀጠልና ማስፈጸም ሲገባቸው፤ የአሁኗ ኤርትራና ሌሎች ቦታዎችን ጭምር ለጣሊያን ሸጠውላቸዋል፡፡

አጼ ምኒልክ፤ ኤርትራን በተመለከተ ብቻ ሰባት የተለያዩ ውሎችን መፈራረማቸውን የሚገልፁት ዶ/ር ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴ፤ ከተለያዩ ምንጮች የተገኙ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ፤ “የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግጭት፤ መንሥኤ እና መፍትሔ” ሲሉ በሰየሙት መጽሐፋቸው ላይ ጠቁመዋል (ገጽ፣ 23)፡፡ በተጨማሪም፤ አጼ ምኒልክ ከእንግሊዝ ጋር የሱዳንና የኢትዮጵያን ድንበር አስመልክተው በ1902 ዓ.ም ባደረጉት ስምምነት፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃና በመጋቢ ወንዞቹ ጭምር የመጠቀም መብቷን የሚያስተጓጉል ውል ተፈራርመው ነበር (ኃይሉ ወልደ ጊዮርጊስ፤ 2001 ዓ.ም፤ ለዓባይ ውሃ ሙግት፤ ገጽ 101)፡፡

በተቃራኒው፤ አጼ ዮሓንስ ከውጪ ኃይሎች ጋር ያደረጉት አንድ ብቸኛ ስምምነት ‹‹የሂወት ውል›› ሲሆን፤ይህም ከላይ እንደተመለከትነው ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ የተወሰዱ ቦታዎችን ለማስመለስና የሐገሪቱን ጥቅምና መብት ለማስጠበቅ የተደረገ ውል እንጂ ኢትዮጵያን የሚጎዳና የሚያስደፍር ውል አልነበረም፡፡

እንደሚታወቀው፤ አጼ ዮሓንስ ቦገስን ለማስመለስ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ ቦገስን ማግኘት አልቻልንም። በሌላ በኩል፤ አጼ ምኒልክ ተዋውለው የሸጧቸው በሰሜንና በምስራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙ ወሳኝ ቦታዎችንና ወደቦችን እስከ አሁን ማስመለስ አልቻልንም፡፡ አጼ ምኒልክ በአባይ ወንዝ ውሃ የመጠቀም መብታችን ላይ የፈጠሩት እክልም እስከ አሁን ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ በአጠቃላይ፤ ቦገስን መልሰን ማግኘትና አጼ ምኒልክ ተዋውለው የሸጧቸውን መሬቶች ማስመለስ አለመቻላችን ከሐገሪቱና ከህዝቡ አቅም ማጣት ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ሆኖም፤ እንደ ግለሰብ ተጠያቂ የሚሆን ሰው ካለ፤ ጥፋተኛውና ተጠያቂው አጼ ምኒልክ ናቸው፡፡

ነገር ግን ፕሮፌሰር መስፍን፤ “ከሁሉም በፊት ቦገስ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳል ማለት ቀድሞውንም የኢትዮጵያ ነበር ማለት ነው፤ ይህ ከሆነ ቦገስ በግብጽ ወይም በብሪታንያ ስር ወድቆ የቀረው የማን ሃላፊነት ነው? በአጼ ዮሐንስ የሆነ ነው” (ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም፤ 2005 ዓ.ም፤ መክሽፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ 110) ይላሉ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን፤ ቦገስ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅኝ ገዢዎች(በግብጽ ወይም በብሪታንያ) ስር የወደቀችው “በአጼ ዮሐንስ ነው” ሲሉ፤ ከአጼ ዮሐንስ በፊት የነበረችውን ኢትዮጵያ ታሪኳን በትክክል አያውቋትም ባይባልም በቅን ልቦና ተመልክተው በነጻ አእምሮ አልፈረዱም ማለት ግን ይቻላል፡፡

ቦገስ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል አካል እንደመሆኗ መጠን፤ ለተለያዩ የውጪ ወራሪ ኃይሎች ተጋላጭ ነበረች፡፡ የእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት በጀመረበት ወቅት በዐረቦች ተጽዕኖ ምክንያት ቦገስ ሁለት ወይም ሦስት ምዕተ ዓመታት ለሚሆን ጊዜ፤ ለማንም ሳይገብሩ ራሳቸውን ያስተዳድሩ በነበሩ ሼኮችና በቱርክ ትተዳደር እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

የጥንቱን ትተን የቅርብ ዘመኑን ታሪክ ማየት እንችላለን፡፡ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ፤ ዶክተር ዋልሄልም ሺምበር የተባለ አንድ ፀሐፊ ለሐገሩ መንግስት (ለጀርመን) የጻፈውን ራፖር መመልከት ይቻላል፡፡ ይህን ራፖር በተመለከተ አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፤ በ“አጼ ዮሐንስ እና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚል መጽሐፋቸው ከዘገቡት ከፊሉን ብቻ ስንመለከት፤ ‹‹….እነዚህ የቦጐስ ወረዳዎች የማን ናቸው? ለሚለው ጥያቄ የጥንት የአበሻ ግዛት መሆናቸው ባይካድም ከ8 እና ከ10 ዓመታት በፊት ደጃች ኃይሉ አባ ሐባል የሚባለው የሐማሴን ባላባት ባጼ ቴዎድሮስ ላይ ስለ ሸፈተና የቃል ኪዳን ጓደኛ ስለፈለገ፤ ቦገስንና ሐልሐልን በጽሑፍ አድርጎ ለግብጽ ገዥ ለቆለታል›› (ገጽ፣ 97) የሚል ቃል ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ ስለዚህ፤ ቦገስ ከአጼ ዮሐንስ በፊት ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ስር እንዳልነበረች ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡

አጼ ዮሐንስ ንጉሠ ነገስት ሆነው ኢትዮጵያን ሲረከቧት፤ እሳቸው የሚመኟት ኢትዮጵያ አልነበረችም። የማነ ገ/መስቀል፤ ‹‹ባሻይ አውአሎም እና የኢትዮጵያ ስለላ ታሪክ›› (2003 ዓ.ም) ሲል በጻፈው መጽሐፍ እንደ ተጠቀሰው፤ እንዲሁም በላይ ግደይ፤ ‹‹ኢትዮጵያ ሀገሬ እና ትዝታዬ›› በሚል ከፃፉት መጽሐፍ እንደተመለከተው፤ አጼ ዮሐንስ፤ ‹‹ሐገራችን የምንላት ከምጽዋ እስከ አትባራ፤ ከበርበራ እስከ ገዳሪፍ፤ ከጋምቤላ እስከ ከሰላ ያለችውን ኢትዮጵያን ነው›› (ገጽ 48) 17 እያሉ ይጠቅሷት የነበረችን ኢትዮጵያ አልተረከቡም፡፡ ሆኖም፤ አጼ ዮሐንስ ሌሎችን በማስወንጀል ተቆራርጣ የተረከቧት ኢትዮጵያን እያስተዳደሩ በዘዴ መኖርና ለትውልድ ማስረከብ ህሊናቸው አልፈቀደም፡፡ ያች በህሊናቸው የሳሏትን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግና ነጻነቷን ለማስጠበቅ ከሞት ውጪ የሚያስቆማቸው ኃይል አልነበረም፡፡

አጼ ዮሐንስ “ለሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የብረት አጥር ሆነው የቆዩትን ጀግና፤ ራስ አሉላ አባ ነጋን ገሸሽ በማድረጋቸው የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል በር ለኢጣልያኖች ከፍቷል” ይላሉ ፕሮፌሰር መስፍን፤ አጼ ዮሓንስን ጥፋተኛ ሲያደርጉ፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የሂወት ውል ከእንግሊዝ ጋር ተዋውለው ስለነበር፤ የራስ አሉላን ለጦርነት መቸኮል አጼ ዮሐንስ አይወዱትም ነበር። ሆኖም፤ በውላቸው መሰረት ማግኘት የሚገባቸውን ነገር ሁሉ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እየጠየቁ እንደነበር፤ ለእንግሊዝና ለአጼ ምኒልክ ከላኳቸው ደብዳቤዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ አጼ ዮሐንስና ራስ አሉላን ለማጣላት በውጪ ወራሪ ኃይሎችና በኢትዮጵያዊያን መኳንንቶች ያልተቆፈረ ጉድጓድ አልነበረም፡፡ ነገር ግን፤ በሁለቱ መካከል የነበረው መተማመንና ግንኙነት ጨርሶ ሊደፈርስ አልቻለም ነበር፡፡ አጼ ዮሐንስ ከሞቱ በኋላ፤ ራስ አሉላ የአጼ ዮሐንስን አልጋ ወራሽ የነበሩትን ራስ መንገሻን ለማንገስ እስከ መጨረሻ ጥረት ማድረጋቸውም የሁለቱን ግንኙነት ጥንካሬ ማሳያ ነው፡፡

በተጨማሪም፤ ፕሮፌሰር መስፍን፤ “…..የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል በር ለኢጣልያኖች ከፍቷል….” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ክፍል በተለያዩ ጊዚያቶች በተለያዩ የውጭ ወራሪዎች መያዛቸው ይታወቃል፡፡ ለአብነት፤ ሱአኪምና የምጽዋ ወደቦች ከ16ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ በቱርክ ቁጥጥር ሥር እንደነበሩ፤ በኋላም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር (እአአ) በ1866 ዓ.ም ቱርክ እነዚህን ወደቦች ለግብጽ እንዳስተላለፈች፤ እንግሊዞች ደግሞ በበኩላቸው በ1885 ዓ.ም ለጣልያኖች እንዳስረከቡ፤ በተጨማሪም ጁሰፔ ሳፔቶ የተባለ ጣልያናዊ ረባቲኖ በተባለ የመርከብ ኩባንያ ስም በ1861 ዓ.ም ከአካባቢው ሡልጣኖች አሰብን ገዝቶ በተዘዋዋሪ በጣልያኖች ቁጥጥር ሥር ማድረጉ ለፕሮፌሰር መስፍን የተሰወረ ታሪክ ሊሆን አይችልም፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የጂኦግራፊ ባለሙያ እንደመሆናቸው መጠን፤ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ወደቦችና ሌሎች ቦታዎች በየትኛው ሀገር ሥር ይተዳደሩ እንደነበር እንደሚያውቁ እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ነገር ግን ፕሮፌሰር መስፍን አጼ ዮሓንስን በማጥላላት አጼ ምኒልክን ለማሞገስ ስለፈለጉ እውነቱን ማድበስበስ ፈልገዋል፡፡ ሆኖም፤ በሰሜን በኩል የምጽዋ፣ የሱአኪምና የአሰብ ወደቦችና ሌሎች ቦታዎች በተለያዩ የውጭ ወራሪዎች (በተለይ በጣልያኖች) ቁጥጥር ስር መውደቃቸው፤ ለኢትዮጵያ በጣሊያን መወረር ዋነኛ ምክንያት አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ በጣሊያን መወረር ዋነኛ ምክንያት፤ ንጉስ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት ከመሆናቸው በፊት ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘት ብለው የሐገሪቷ እምብርት በሆነው በሸዋ “ልጥ ማረፍያ” በተባለ ቦታ የጣሊያን ሰላዮችን ማስጠጋታቸውና ቦታ መስጠታቸው ነበር፡፡ ለዚህ ዋቢ ሊደረግ የሚችለው፤ ትራቬርሲ የተባለ ጣልያናዊ‹‹……ወደ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ሊቢያ ልንደርስ የቻልነው፤ እንዲሁም ጣሊያኖች የቅኝ ግዛት ስሜትእንዲያድረባቸው ያደረገየፖለቲካ ሥራ የመጀመርያ ጮራ የፈነጠቀው ከልጥ ማረፍያ ነው›› (ዶ/ር ተወልደ ትኩእ፤ 1990 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያ አንድነት እና ኢጣሊያ፤ ገጽ 230) ሲል መግለፁ ነው፡፡ ምክንያቱም ጣሊያኖች ‹‹ልጥ ማረፍያ›› መቀመጥ በመቻላቸው፤ ስለአገሪቷ ሁለንተናዊ (ማለትም ጂኦግራፊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ) ሁኔታዎች በሚገባ የማጥናት ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡

በመጨረሻም፤ አጼ ዮሐንስ ‘እንደ ዳዊት በዓይነ ህሊናዬ እያገላበጥኩ የምደግማት ኢትዮጵያን ሲነኩብኝ ደሜ ይፈላል ’22 ብለው ለሚገልጿት ውድ ሀገራቸው፤ ነጻነቷ ጠብቀው፣ አንድነቷን አጠንክረውና አደልድለው ለትውልድ ለማስተላለፍ፤ ከዳር እስከዳር እየተወረወሩ ያልከፈሉት ዋጋ እንደሌለ ጠላቶቻቸውም ጭምር መስክረውላቸዋል፡፡ ታዲያ፤ ፕሮፌሰር መስፍን የውጭ ጠላቶች ጭምር የመሰከሩላቸውን ለሐገራቸው ነፃነት ቀናኢ የሆኑትን የአጼ ዮሐንስን ማንነት ለማጉደፍ የሚያደርጉት ጥረት ምን ዓላማ ይኖረው ይሆን?
መቼም ታሪክ ያለፈ ሁነት ነው፡፡ ስለሆነም ለቀጣይ ትውልድ መንደርደሪያና ማስተማርያ እንጂ እንደ ልብወለድ ድርሰት ሊታረምና ሊጠገን የሚችል ነገር አይደለም፡፡ ትክክለኛ ታሪክ ለትውልድ ማስተላለፍ የቀደምት ትውልዶች የግዴታ ስራ መሆኑ የሁላችንም እምነት ነው፡፡ ሆኖም፤ የጥንካሬያችን ማሳያ ሊሆን የሚችለው እምነታችንን በተግባር ስንፈጽም ብቻ ነው፡፡

ስለኢትዮጵያ ታሪክ የታሪክ መጻሕፍት ሳነብ አጼ ዮሐንስን የሚገልጽልኝ ቃልም ሆነ ዐረፍተ ነገር ላገኝ አልቻልኩም ነበር፡፡ በመሆኑም የርሳቸውን ሰብዕና የምገልጽበት ቃል እቸገር ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን፤ ዶ/ር ገላውዲዎስ አርአያ በ2006 ዓ.ም (The Martyred King of Kings: Emperor Yohannes IV of Ethiopia, Institute of Development and Education for Africa (IDEA፣ ) በሚል ርዕስ፤ ስለአጼዮሐንስ የፃፉትን አንድ መጣጥፍ ሳነብ ያገኘኋት አንዲት ዐረፍተ ነገር፤ የአጼ ዮሐንስን ሰብዕና በደንብ ስለገለጸችልኝ ደስታ ተሰማኝ፡፡ ሆኖም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እንዳልጣላ ተጨነቅኩ፡፡ በመጨረሻም እውነታው መቀበል እንዳለብኝ አመንኩ፡፡ ስለዚህ ሌሎች የአገሬ ሰዎች እንደማይቀየሙኝ ተስፋ በማድረግ፤ በተዋስኳት የእንግሊዝኛ ዐረፍተ ነገር አጼ ዮሐንስን ለመግለጽ ወደድኩ፡፡ ቃል በቃል ሲቀመጥ፤ ‘By his utmost commitment to his people and his country and his indefatigable patriotism, Yohannes makes every Ethiopian a dwarf-thinking animal›› ይላል፡፡
(ውድ አንባቢያን፡- – ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻ Email: romha79@gmail.com
ማግኘት ይቻላል፡፡)

ገ/መድህን ሮምሃ (ዶ/ር) – ዲላ ዩኒቨርስቲ

You may also like...