abrahaDesta

ወልቃይት ወዴት ይካለል?

“ወልቃይት የወልቃይት ነው። ወልቃይት የኢትዮጵያ ነው” የሚል አቋም በያዝኩበት ጉዳይ ላይ ብዙ አቧራ ማስነሳቱ ይታወሳል። ወልቃይት የአማራ ወይ የትግራይ ነው በል የሚል ሓሳብም ተቀብያለሁ። ዛሬ ጓደኛዬ ዳንኤል ሺበሺ በዚህ አቋሜ ላይ በሰጠው ነቀፌታ ማብራርያ እሰጣለሁ።

ዳንኤል ፅሑፉ ሲጀምር አብረን ስለመታሰራችን ይጠቅሳል። እኔ የታሰርኩት ወደ ብሄርና ጎሳ የወረደ አቋም ባለመያዜ ነው። በማእከላዊ ምርመራ ወቅት ከፍተኛ የደህንነት ሰዎች ሲጠይቁኝ የነበረው “የትግራይን ህዝብ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ ታፍኗል፣ ተጨቁኗል ብለህ መፃፍ ለምን አስፈለገህ?” የሚል እና “በኢትዮጵያ ደረጃ የሚንቀሳቀስ ሀገራዊ ፓርቲ ለማቋቋም ስትንቀሳቀስ ነበር” የሚሉ ነበሩ። (የሚገርመው ሽብርን የተመለከተ ጥያቄ አልተጠየቅኩም)።

እናም የታሰርኩት “ኢትዮጵያዊነት” በሚል አቋሜ ነው። ሁሉም ሰው ሳይከፋፈል በእኩል ዓይን እንየው በሚል ዓቋሜ ነው። ሁሉም ሰው ብሄር፣ ቋንቋ፣ ሀይማኖት ወዘተ ሳይለይ ነፃነቱ ማግኘት አለበት ስላልኩ ነው የታሰርኩ። የታሰርኩት ኢትዮጵያ ሀገሬ ላይ ስለተንጠላጠልኩ እንጂ ወደ ወረዳ በመውረዴ አይደለም። ከኢትዮጵያዊነት ወደ ጎሳ ወይ ወረዳ ወርጄ እገሌ ወረዳ የእገሌ ነው፣ እገሌ ህዝብ ጠላት ነው፣ እነ እገሌ እንዲህ ናቸው ወዘተ ብዬ ወደ ህወሓት ደረጃ ብወርድ ኑሮ አልታሰርም ነበር። ምክንያቱም በወረዳ ደረጃ ተገኝቼ ወልቃይት የትግራይ ነው ብል ኑሮ ህወሓት አያስረኝም ነበር። ምክንያቱም የህወሓት አቋምና ደረጃ ነው። ህወሓት በራሱ ደረጃ (ሜዳ) ማሸነፍ አልችልም። የማላሸንፈው ከሆነ ለምን ይሰጋል? ካላሰጋሁት ለምን ያስረኛል? ወልቃይት የአማራ ነው ብልም አያስረኝም። ምክንያቱም በቀላል የማጥላላት ፕሮፓጋንዳ ከህዝብ ይነጥለኛል። ከህዝብ ከነጠለኝ እንዴት ላሰጋው እችላለሁ?

ደግሞ ወደ ህወሓት ደረጃ ወርጄ አንድን ህዝብ ከሌላ ህዝብ ጋር የሚያጣላ አቋም ይዜ የህወሓትን አጀንዳ እያስፈፀምኩ ህወሓትን መተቸትና መቃወም እንዴት እችላለሁ? ህወሓት ኢህአዴግን የምቃወምበት መርህ አለኝ። መርሁ የኢህአዴግ አስተሳሰብ፣ አይዲዮሎጂ፣ አካሄድ፣ አሰራር ወዘተ ለኢትዮጵያ ሀገርና ህዝብ ጠቃሚ ስላልሆነ ነው። ለምሳሌ ህወሓት ኢህአዴግ በዘር (ብሄር ወይ ጎሳ) ከፋፍሎናል። እርስበርሳችን እንዳንተማመን አድርጎናል። በኢህአዴግ ዘመን ሰው በሰውነቱ ሳይሆን በአከባቢው፣ በቋንቋው፣ በሀይማኖቱ ወዘተ ይመዘናል፣ አድልዎ ይደርስበታል፣ ህዝብ ከህዝብ እንዳያብር ያደርጋል። እነዚህ ሁሉ የምቃወማቸው ናቸው። እነዚህ ከተቃወምኩ እንዴት ብዬ ነው አማራና ትግራይ የተለያየ እንደሆነ አድርጌ አንድ ወረዳ የእገሌ ነው ወይ አይደለም የምለው? እንዲህ ካልኩ እንዴት የኢህአዴግ ተቃዋሚ እሆናለሁ? ህዝብን አንድ የሚያደርግ እንጂ ህዝብን ከፋፍሎ የሚያጣላ መቼ አነሰናነው?! እንዲህ ካልኩኮ የህወሓት ኢህአዴግ አቋም ነው የማራምደው ማለት ነው። ትግራይን ትተህ ለአማራ ከወገንክ ወይም አማራን ትተህ ከትግራይ ከወገንክ ከህወሓት በምን ተሻልክ? ህወሓትን የምቃወምበት ምክንያት ህወሓት ትግርኛ ተናጋሪ ስለሆነ አይደለም። አማርኛ ወይ ኦሮምኛ ተናጋሪ ስርዓት ሁኖ እንደ ህወሓት አድሎአዊ፣ ከፋፋይና ፀረ ህዝብ አቋም ካለው እቃወመዋለሁ። ተቃዋሚ የሆንኩት ከህወሓት ኢህአዴግ የተሻለ ህዝባዊ መንግስት ለመመስረት እንጂ ሌላ ከፋፋይና ፀረ ህዝብ ስርዓት ለመትከል አይደለም።

ወልቃይት የአማራ ወይ የትግራይ ነው የሚል አቋም ለመያዝ ከህወሓት ባልተነነሳ (በወረደ) ዘረኛ መሆን አለብኝ። ሲጀመር ወልቃይት ማንነቱ እንዲህ ነውና ወዲህ መካከል አለበት ለማለት የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ክልሎች ማንነትን (ብሄርን) መሰረት ያደረገ አከላለል መሆን አለበት የሚል የህወሓት ኢህአዴግ አቋም መደገፍ አለብኝ። ይህን የህወሓት አጀንዳ ሳትቀበል ስለ ወልቃይት ማንነትና ክልል ምርጫ አጀንዳ ማድረግ አይቻልም። ወልቃይት ማንነቱን መሰረት አድርጌ ከወሰንኩ በዘር የመለያየታችንን ጉዳይ መደገፍ ይሆንብኛል። ከዛም ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የመስበክ ሞራል አይኖረኝም። ወልቃይት የዚህ ክልል ህዝብ ወይ መሬት ነው ካልኩ በቡድን መብት ነው የማምነው ማለት ነው። ይህም የኢህአዴግን አብዮታዊ ዴሞክራሲ መቀበል ግድ ይሆንብኛል።

እኔ የማምነው በግል መብት ነው። የግል መብት ከተከበረ የሁሉም መብት (የቡድንም ጨምሮ) ይከበራል። በዚህ እሳቤ ማንኛውም ሰው ወይ ህዝብ የፈለገውን ማንነት የመያዝ ነፃነት ይኖረዋል። መሬትም የሀገርና የግለሰብ ይሆናል። ክልሎች የአንድ ሉአላዊ ሀገር አስተዳደራዊ መዋቅሮች እንጂ ራሳቸው የቻሉ ሀገሮች አይደሉም። እናም ክልሎች ሉአላዊ ሀገሮች (ነፃ ሀገሮች) እስካልሆኑ ድረስ የራስቸው ግዛት (መሬት) አይኖራቸውም። መሬት ወይ ግዛት የሉአላዊነት መገለጫ ነው። ስለዚህ ትግራይና አማራ ተገንጥለው ነፃ ሀገር እስካልሆኑ ድረስ ወልቃይት የትም ቢሆን (ከኢትዮጵያ እስካልወጣ ድረስ) ግድ የለኝም። እኔ በብሄር (በክልል) አላምንም። ኢትዮጵያዊ ነኝ። እናም አምራና ትግራይ ለኔ እኩል ናቸው። የህወሓትን አጀንዳ እያራመድኩ ህወሓትን መቃወም አልችልም።

ስለዚህ ወልቃይት የማነው የሚለው ጥያቄ ለኔ ትርጉም የለውም። ኢትዮጵያ አንድ ነች። የህዝብ ጥያቄ ግን አለ። ማንኛውም የህዝብ ጥያቄ መልስ ይሻል። መልሱ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት። ለምሳሌ የወልቃይትን ህዝብ ጥያቄ የማንነት ነው ካልን ጥያቀው ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ግድ ነው። ለምንስ ተጠየቀ መባልም አለበት። ምክንያቱም አንድ ችግር ለመፍታት ዋናው መንስኤ ማወቅ አለብህ።

እንበል የወልቃይትን ህዝብ እየጠየቀኝ ነው። ጥያቀያቹ ምንድነው? የማንነት ጥያቄ ነው (እንበል)። ማንነታቹ ምን ሆነ? የፈለጋችሁትን ማንነት የመያዝ መብታቹ አልተከበረም? ከፈለጋቹ አማራ ከፈለጋቹ ትግራይ ከፈለጋቹ ወልቃይት ከፈለጋቹ … የመሆን መብታቹ አልተከበረም? መልሱ አዎ የሚል ከሆነ የመብት ጥሰት እንደሆነ እረዳለሁ። ስለዚህ ለመብት ረገጣ መፍትሔው ምንድነው? ትግል ነው። አብረን እንታገል፣ መብታችንን ለማስከበር። መልሳቸው “አዎ” የሚል ሳይሆን “አይደለም” ከሆነ ግን ጥያቄ የላቸውም ማለት ነው።

“አይ! ጥያቄው ኮ እኛ አማራ ወይ ትግራይ ስለሆንን ወደ አማራ ወይ ወደ ትግራይ ነው መካለል የምንፈልገው” የሚል ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ የማንነት ሳይሆን የአከላለል ነው ማለት ነው። ምክንያቱም የማንነት ጥያቄ ከሆነ የትም ሁነው ሊመለስላቸው ይገባል። የአከላለል ጉዳይ ከሆነ የአስተዳደር ጉዳይ ነው ማለት ነው። ወደ አማራ ወይ ወደ ትግራይ ክልል መሆን ነው የምንፈልገው ብለው ሲሉ አስተዳደራቸው ከአማራ ክልል ወይ ከትግራይ ክልል ጋር መሆን አለበት እያሉ ነው። ይህም ዴሞክራሲያዊ መፍትሄ ይሰጠው። ዴሞክራሲ ምንድነው? ዴሞክራሲ የህዝብ መንግስት ማለት ነው። የህዝብ መንግስት ማለት የህዝብ ድምፅ የሚሰማበትና የሚወስንበት አካሄድ ማለት ነው። ስለዚህ ህዝቡ ከነማን ጋር መካከል እንዳለበት ራሱ ህዝቡ እንዲወስን መፍቀድ ነው።

“ወልቃይት” ስንል ግን ማንን ማለት ነው? ወልቃይት ህዝብ ነው ወይስ መሬት? በተደጋጋሚ ጠይቄ አልተመለሰልኝም። ወልቃይት ህዝብ ከሆነ ወልቃይት የሚባል ማንነት ያለው ህዝብ አለ ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ወልቃይት የሚባል ህዝብ ራሱን ችሉ ማንነቱን ጠብቆ ወደ ፈለገው መወሰን ይችላል። ወልቃይት የሚባል ህዝብ ከሌለ (ህዝቡ አማራ ወይ ትግራይ እንጂ ወልቃይት የሚባል ህዝብ ከሌለ) ግን ወልቃይት የመሬት ስም ነው ማለት ነው። ወልቃይት የመሬት ስም ከሆነ ማነው የሚወስነው? እዛው ወልቃይት የሚኖር ህዝብ ድምፁን ሰጥቶ ወዴት እንደሚፈልግ ይወስን።

ዳንኤል በወልቃይት ጉዳይ የሁለቱም ህዝቦች (የአማራና የትግራይ) ግንኙት በደቡብ አፍሪካውያንና በእንግሊዞች ግንኙነት ለማመሳሰል የሞከረው አልተመቸኝም። ትግራይና አማራ;ኮ አንድ ህዝብ ነው፣ አንድ ሀገር ነው። አብሮና ተከባብሮ ለዘመናት የኖረ ህዝብ ነው። የአውሮፓዊና የአፍሪካዊ ያህል ልዩነት የለውም። የወልቃይት ጥያቄ ከባድመና (ኢትዮ ኤርትራ) ወይ እየሩሳሌም (እስራኤልና ፍልስጤል) ጉዳይ ጋር አይነፃፀርም። ምክንያቱም እነዛ ሉአላዊ ሀገሮች ናቸው። አማራና ትግራይ ግን አንድ ሀገር ናቸው። ስለዚህ ለማንም ሳናዳላ ህዝብ የሚጠቀምበት መንገድ ነው ማፈላለግ ያለብን። ሁሉም ነገር ከእናት ሀገር ኢትዮጵያ ነው ማየት ያለብን። ስለብሄራዊ ጥቅም የሚነሳው ስለ ል አላዊነትና የሀገር ግዛት ሲነሳ ነው።

ሌላው ማብራርያ የሚያስፈልገው ጉዳይ ጎንደር ክፍለ ሀገርና ትግራይ ክልል በማነፃፀር የሚደረግ የይገባኛል ጥያቄ ነው። በመጀመርያ የኔ አቋም ወልቃይት የማነው ሳይሆን ወልቃይት ወዴት ይካለል የሚል መሆን አለበት ነው። ወዴት ይካለል ለሚለው መልሱ በዴሞክራሲያዊ አገባብ በህዝበ ዉሳኔ ይሆናል የሚል ነው። የመጨረሻው የዴሞክራሲ ዉሳኔ ህዝበ ዉሳኔ ነውና። ወልቃይት የትም ቢካለል ጉዳዬ አይደለም። የኔ ጉዳይ የወልቃይትን ህዝብ በፈለገውና በፈቀደው ክልል ሲተዳደር ነፃነቱ ተከብሯል ወይ? ፍትሓዊ ልማት እያገኘ ነው ወይ? የሚል ነው።

ወደ ጉዳዩ ልመለስ። ወልቃይት ወደ ትግራይ መካለሉ የሚቃወሙ ሰዎች ወልቃይት ድሮ ጎንደር እንደነበር ይጠቅሱና በታሪክ የትግራይ ክልል አካል ሁኖ እንደማያውቅ የታሪክ ሰዎችና የቀድሞ አስተዳዳሪዎች ጠቅሰው ይዘግባሉ። ለምሳሌ “ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ወልቃይት የትግራይ ክልል እንዳልነበረ መስክረዋል” የሚል ሓሳብ ያነሳሉ።

ሲጀመር ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ትግራይ ክልልን አስተዳድረው አያውቁም። ትግራይ ክልል ከተመሰረተ ገና ሃያ አምስት ዓመቱ ነው (የትግራይ ክልል፣ የትግራይ ህዝብ አላልኩም) ። የመጀመርያ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ አቶ ገብሩ አስራት፣ ከዛም አቶ ፀጋይ በርሀ፣ ከዛም አቶ አባይ ወልዱ ናቸው። ራስ መንገሻ ስዩም ያስተዳደሩት ክልል አይደለም፤ ክፍለ ሀገር ነው፤ የትግሬ ክፍለ ሀገር። የትግሬ ክፍለ ሌላ ነው። ገዢዎች ለራሳቸው በሚጠቅም መልኩ አስተዳደሮች ይከልላሉ። አፄ ሀይለስላሴ ለራሱ ዓላማ ሲል (ለህዝብ ብሎ ሳይሆን) የራሱ አስተዳደር አዋቅሮ ኢትዮጵያ በክፍለ ሀገሮች አዋቅሯታል። ኢህአዴግም እንደዙ ለህዝብ ብሎ ሳይሆን ለራሱ ጥቅም ሲል የመረጠውን አከላለል ተጠቅሞ ሀገራችን በክልሎች ከፋፍሏታል። በሀይለስላሴና በኢህአዴግ የሚታይ አከላለል ይለያያል፤ ዓላማው ግን አንድ ነው፤ የገዢዎችን ጥቅም ማስከበር።

እናም ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ሲከልል በፊት የነበሩ ክፍለ አሀገሮችን ቀያይሯቸዋል። ለምሳሌ ትግሬ ክፍለ ሀገር የነበረውን ግማሹ ወደ ትግራይ ክልል ግማሹ ደግሞ ወደ ዓፋር ክልል አድርጎታል። ጎንደር ክፍለ አሀገርም ግማሹ ወደ አማራ ግማሹ ወደ ትግራይ፤ ወሎ ክፍለ ሀገር ግማሹ ወደ አማራ ግማሹ ደግሞ ወደ ዓፋር፤ ሸዋ ክፍለ ሀገር ግማሹ ወደ አማራ ግማሹ ደግሞ ወደ ኦሮምያ ወዘተ በማድረግ አዲስ የክልሎች አወቃቀር አሳይቶናል።

ወልቃይት ከጎንደር ወደ ትግራይ ክልል ተወሰደ ሳይሆን ተካለለ መባል አለበት፤ ልክ ዓፋር ከትግሬ ወደ ዓፋር ወይም ኣምቦ ከሸዋ ወድ ኦሮምያ እንደተካለለ። ወልቃይት የጎንደር ክፍለ ሀገር ነበር አሁን ግን ከትግራይ ክልል ጋር ነው። ሰመራ የወሎ ክፍለ ሀገር ነበር አሁን ግን ዓፋር ነው። አምቦ ድሮ ሸዋ ክፍለ ሀገር ነበር አሁን ግን ኦሮምያ ክልል ነው። አጠቃላይ የኢህአዴግን አከላለል መቃወም ይቻላል። ስንቃወም ክልል መኖር የለበትም ብለን አይደለም። የአካለሉ ጉዳይ ነው መቃወም የምንችለው። የአከላለሉ መስፈርት ወስደን ለህዝብ የማይጠቅም ከሆነ ወይ የህዝብ ፍላጎት መሰረት ያደረገ ካልሆነ ወይም የኢትዮጵያ ወይ የህዝብ አንድነት አደጋ ዉስጥ የሚከት ከሆነ መቃወም እንችላለን። የአካለል መስፈርቱ ግልፅና ለሁሉም የሚሰራ መሆን አለበት።

አሁን ወልቃይት በታሪክ የጎንደር ክፍለ ሀገር እንደነበር ማስረጃዎችን አስባስበህ በዚሁ መሰረት ወልቃይት የአማራ ክልል ነው ለማለት የሚቻል አይደለም። ወይስ ወልቃይት በአፄዎቹ ግዜ የጎንደር ክፍለ ሀገር ስለነበረ ወደ ድሮ የክልሎች አወቃቀር እንመለስ እየተባለ ነው? የድሮ አወቀቀር ይሻላል ከሆነ ከነ ምክንያቱ ይቅረብ። ከዛም ለሁሉም ክልሎች ይስራ። ምክንያቱም ሁሉም ክልሎች አዲስ ናቸው። በድሮ ግዜ የነበረ አሁንም ቅርፁ ሳይቀር ያለ የለም። ትግራይ አዲስ ነው። አማራም አዲስ ነው። ኦሮምያም አዲስ ነው። ዛሬ በታሪክ ወልቃይት የትግራይ ክልል ሁኖ አያውቅም ብለህ ካስመሰከርክ ነገም በታሪክ (በአፄዎቹ አገዛዝ) ኦሮምያ የሚባል ክልል አነበረም፤ አምቦ የሸዋ ነበር፤ ስለዚህ አምቦ ወደ —— ይመለስልን ሊባል ነው።

ጎንደር ክፍለ ሀገር (የአፄዎች)ና ትግራይ ክልል (የኢህአዴግ) ማወዳደር ስህተት ነው። ምክንያቱም አንድ እግርህ ሀይለስላሴ ጋ አንድ እግርህ ደግሞ ኢህአዴግ ጋ ረግጠህ መቆም አያዋጣም። የኢህአዴግን አወቃቀር ጠልተን የድሮ የክፍለ ሀገር ታሪክ ነው የሚሻለን ካልን አንድ ነገር ነው። ሁሉም ክልሎች ወደ ነበሩበት ይመለሱ ልንል ነው። ስለዚህ አቋማችን ግልፅ መሆን አለበት። የአወቃቀር መስፈርቱ መተቸት አንድ ነገር ነው። ወደ ድሮ እንመለስ ደግሞ ሌላ ነገር ነው።

በወልቃይት ጉዳይ ታሪክ ማንሳት ልክ አይደለም። የድሮ ልክ ነው ብለን ታሪክን አስታውሰን አንድ መሬት ወደነበረበት ለመመለስ ከታገልን አሁን ያሉት ዘጠኝ ክልሎች በሙሉ ልናፈርሳቸው ነው። ምክንያቱም ሁሉም ክልሎች አዲስ ናቸው። ያልተበተነ የድሮ ክፍለ ሀገር የለም። ታሪክ እንደ ዋነኛ መስፈርት መግባት አለበት ካልን ደግሞ አጠቃላዩን የኢህአዴግ የአከላለል መስፈርት መተቸት ይቻላል።

ዋናው ሓሳብ የወልቃይት ጉዳይ ከኢትዮጵያዊነት ወደ ወረዳነት ያወርደናል። ከሀገራዊነት ወደ ጎሳነት መውረድ ወደ ኢህአዴግ ሜዳ መግባት ነው። በኢህአዴግ ሜዳ ተጫውተን ኢህአዴግን ማሸነፍ አንችልም። ኢህአዴግን ካላሸነፍን ነፃነታችንን ማግኘት አንችልም። ነፃነታችንን ካላገኘን የምንፈልገው ዓይነት አስተዳደር ማግኘት አንችልም። ጨቋኙን ስርዓት በማናሸንፍበት መንገድ ለምን እንጓዛለን??? ምክንያቱም ኢህአዴግን እየተቃወምክ የኢህአዴግን አጀንዳ ማራመድ የምትቃወመውን መደገፍ ነው። እየተቃወምክ መተግበር ከራስ ጋር መጣላት ነው። ከራሱ ጋር ተጣልቶ ራሱን ያሸነፈ የለም። ግልፅ መርህ ሊኖረን ይገባል። መርህ ከሌለን ወዴት እንደምንራመድ አናውቅም። የምንሄድበትን ካላወቅን የትም አንደርስም። ስለዚህ ራሳችን እንፈትሽ።

It is so!!! .

You may also like...